በአለማችን ያሉ ታላላቅ የስደተኞች እና የሰራተኞች ማህበራት አመሰራረት አልጋ በአልጋ ሆኖ እንዳልሆነ እሙን ነው። ማህበራቸውን በሁለት እግሩ ለማቆም የሰው ህይወት፣ገንዘብ፣ ውድ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው እንጂ። በሂደቱም ዳግመኛ ላለመውደቅ የሚረዳቸውን መሰረት ሰፋ አድርግው መስርተው ለሌሎች ጥላና ከለላ ሆነው እነሆ ለሌሎችም እያበሩ ይገኛሉ።
መስዋዕትም ከአንጋፋዎቹ የተማረ፣ በሊባኖስ የኢትዮጵያውያኑ እና ከሌላ አገራት የመጡ ስደተኛ የቤት ውስጥ ሰራተኞች እንግልትና ስቃይ በ2014 እ.አ.አ “መስዋዕት” የተወለደ ማህበርና ሲሆን። በወቅቱም ከ200 ያላነሱ አባላት ነበሩት።
እንግዲህ መስዋዕት ከላይ እንደ ጠቀስነው አርአያ የሆኑትን ድርጅቶች መነሻ አድርጎ ከመነሳቱ በፊት ከ 15 በማይበልጡ አባላቱ የቅስቀሳ፣ ለግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሆኑ አጫጭር ድራማዎችን በተለየያዩ መድረኮች በማዘጋጀት እና ደረጃቸውን የጠበቁ ሙሉ አሰተማሪ ፊልሞችን በመስራት እንዲሁም በውስን አቅሙም በየሆስፒታሉ እና በእስር ቤቶች የነበሩ እህቶችን በመጠየቅና በመደገፍ ከ3 ላላነሱ አመታት ሲታገል ቆይቶ ከላይ እንደ ገለጽነው “መስዋዕት” የሚለውን ስም በማውጣት በወቅቱ ለምስረታውም ሆነ ለተለያዩ ድጋፎች ከጎኑ በነበረው “Migrant workers task force” በኋላም ” Migrant Community Center ” ከለላነት በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ጀመረ።
በነዛ ባሳለፍናቸው ግዜያቶች በተለይ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት ማህበሩ ወደፊት እንዳይሄድ ከፊቱ ከባድ ጋሬጦች ተጋርጠው የነበረበት ቢሆንም በአባላቱ ከፍተኛ ተጋድሎና አልሸነፍ ባይነት ብዙውን ችግር አልፎ ዛሬ ላይ ቆሞ ይገኛል። በወቅቱ ይህ ማህበር ሲያነሳቸው በነበሩ ጠንካራ ሒሶች መነሻነት በሊባኖስ ባለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፍተኛ ጫና ይደርስበት የነበረ እና ማህበሩንም የተቀናቃኝ ፖለቲካ ድርጅት አጋዥ ማህበር ነው በሚል በማህበረሰቡ ዘንድ ውዝግብ እንዲፈጠር ያደረገና አመራሮቹንም ወደ አገራቸው መግባት የማይችሉባቸውን እገዳዎችን አስጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም በአልሸነፍም ባይነት እና በሊባኖስ በቤት ውስጥ ሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ፣ የህይወት መጥፋት እና መከራ ቸል የማይባልበት ደረጃ ደርሶ ስለነበረና አንድ አካልም በጉዳዩ ላይ መንቀሳቀ የነበረበት በመሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ማህበራት ባለመኖራቸው ሳይፈርስ መቆየቱን በመምረጥ ሲታገል ቆይቶ አሁንም በአሸናፊነት እና በአለኝታነት እየታገለ ይገኛል።
መስዋዕት በአሁን ሰአት ምንም እንኳን የምዝገባ ሰርተፍኬት ባይኖረውም በአገሪቱ ላይ ዜጎችን ተኮር የሆነ የነፍስ አድን እና የተለያዩ ገንቢ ስልጠናዎችን ለአባላቱ እየሰጠ እና ወደፊት እየሄደ ያለ ድርጅት ነው።
በመሆኑም በአሁን ሰአት ኢትዮጵያኖች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ቢያንስ መጠነኛ እውቀት ኖሮአቸው ቢሄዱ ራሳቸውን መደገፍ ይችላሉ ብሎ በማሰብ የልብስ ስፌት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል።
እንዲሁም በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን እናቶች በአለባቸው የኢኮኖሚ ችግር ልጆቻቸውን ማስቀመጫ ቦታ ማግኘት ባለመቻላቸው እና መስራት ባለመቻላቸው ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ የበረራ ፕሮጀችት ነድፎ በስራ ላይ አውሎ በጥቂት ህጻናት የልጆች ማቆያ ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል።